አመራሩ ቴክኖሎጂን በአግባቡ የሚጠቀም ትውልድ ለመፍጠር በሚደረገው ጥረት ግንባር ቀደም ሆኖ ሊሰራ እንደሚገባ የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ጌታሁን አብዲሳ ገለጹ
****
(አሶሳ፤ መጋቢት 23/2017 ዓ/ም) በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ዘመኑን የዋጀ ቴክኖሎጂ ተጠቃሚ ትውልድ ለመፍጠር በሚደረገው ጥረት አመራሩ ግንባር ቀደም ሆኖ ሊሰራ እንደሚገባ የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ጌታሁን አብዲሳ ገለጹ።
ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ጌታሁን አብዲሳ፤ በክልሉ ዲጅታል ኢትዮጵያን ለመፍጠር የኮደርስ ዲጂታል ስልጠናን አጠናክሮ ማስቀጠል እንደሚገባ ተናግረዋል።
ስልጠናው በቴክኖሎጂ የዋጀ ትውልድን ለመፍጠርና
ከነበረው ዕውቀት ላይ ተጨማሪ ክህሎት እንደሚያስገኝ ጠቁመዋል።
በተያዘው በጀት ዓመት 16ሺ ሰልጣኞችን ለማሰልጠን ቢታቀድም በሚፈለገው መንገድ ውጤት ማስመዝገብ አልተቻለም ያሉት አቶ ጌታሁን፤ ለውጤታማነቱ አመራሩ ቁርጠኛ ሆኖ ሊሠራ ይገባል ብለዋል።
ወጣቶች ከወቅቱ ጋር ለመራመድ ራሳቸውን በቴክኖሎጂ ማበልፀግ እንዳለባቸውም ጠቁመው ስልጠናው ለቴክኖሎጂ ሽግግር አስተዋጽኦ እንዳለው አስገንዝበዋል።
እንደ ሀገር ለሦስት ዓመታት የሚሰጠው ይህ የኮደርስ ዲጅታል ቴክኖሎጂ ስልጠና ወጣቱን ኃይል ይበልጥ ተጠቃሚ ለማድረግ ያለመ መሆኑንም ጠቅሰዋል።
የክልሉ የሳይንስ ቴክኖሎጂና ኢንፎርሜሽን ኮሚኒኬሽን ኤጄንሲ ዳይሬክተር አቶ ይታያል በላይ በበኩላቸው፣ ለስልጠናው ተደጋጋሚ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎች መስራት መቻሉን ገልጸዋል።
የሚሰጡ ስልጠናዎችም ሥራዎችን በጥራት፣ በፍጥነት እና ወጪ ቆጣቢ በሆነ መልኩ ማከናወን እንደሚቻል የተናገሩት ዋና ዳይሬክተሩ፣ ወጣቱ ትውልድ ዘመኑን የዋጀ የቴክኖሎጂ ተጠቃሚ እንዲሆን በየደረጃው የሚገኝ አመራር በጎ አስተዋጽኦ ሊያደርግ ይገባል ብለዋል።
ስልጠናውን ተደራሽ ለማድረግም በሁሉም ዞኖች፣ ከተማ አስተዳደሮች እና ወረዳዎች የግንዛቤ ፈጠራ ስራው ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።
በክልሉ በቀጣዮቹ ሶስት ዓመታት ከ65 ሺ በላይ ወጣቶች የኮደርስ ስልጠናውን ይወስዳሉ ተብሎ ይጠበቃል።


